የአዳብና ክብረ በዓል በሶዶ ክስታኔዎች
ሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ በጉጉት ከሚጠበቁየወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ጨዋታዎች መካከል አዳብናአንዱና ዋነኛው ነው።ይህ የወጣት ወንዶች ልጃገረዶች ጨዋታ ከመስቀል ደመራ ዕለት ጀመሮ እስከ ጥቅምት አምስት በየገበያስፍራዎችና በየደብሩ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ይቀጥላል።አዳብና ከመድረሱ በፊት ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች በተለያየመንገድ አዳብናን ለማክበር ይዘገጃጃሉ።ያላገቡ ወጣት ወንዶች የቡሄ ዕለት በየአባቢያቸው ባለ ሰፊ መስክ ላይደመራ(ምጅር)ያቆማሉ። በዛው ክረምቱ ማለፉንም ጅራፍ በመተኮስ ያበስራሉ።ሆያሆሄም በመጨፈር አደብና ጨዋታ ላይ ልባቸው ለከጀላት ኮረዳ ስጦታ ገዝቶ(ሎሚ ፣ማስቲካና መሰል ነገሮችን)ለመስጠት ገንዘብያጠራቅማሉ።
ልጃገረዶችም በበኩላቸው በአዲስ ዓመት ዋዜማቀን” አዬ አዬ ሆ አዬ አዬ ሆ አዬ ንብለ” እያሉ እንጊጫ በመንቀልና ለአዲስ አመት እንቁጣጣሽ በመጨፈር ለአዳብናቸው ገንዘብያጥራቅማሉ ፣ የአዳብና ዕለት አምሮ ለመታየት አዲስ ልብስናጌጣጌጣቸው ያዘጋጃሉ ፣ ፀጉራቸውን በልዩ ሁኔታ ይሰራሉ።ወንዶችም ሴቶችም ከአዲስ ዓመት(አክራሚ) ዋዜማ ቀን ጀምሮመስቀል እስኪደርስ ድረስ በየአካባቢው ባቆሙት ደመራ(ምጅር)ምሽት ምሽት ተሰብስበው ይጨፍራሉ።
ይህ አዳብና ከመድረሱበፊት ጓደኝነታቸው የሚያጎለበቱበት አዳብና የት የት እንደሚሄዱየሚቀጣጠሩበት ጊዜ ነው።እንዲሁም ታዳጊ ልጆች አጨፋፈሩን የሚማሩበትና ልምድ የሚወስዱበት ጊዜም ጭምር ነው።አዳብና ላይ የተለያዩ የጨዋታ ዓይነቶች ሲኖሩ ወንዶችናልጃገረዶች አብረው ክብ ሰርተው ወንዶች በጉረሮ በሚያወጡትልዩ ድምፅና በጭብጨባ ፤ልጃገረዶቹ በከበሮና በጭብጨባ የተወሰኑት ወንዶችና ልጃገረዶች ደግሞ በክቡ መሃል በመግባትና በመጨፈር የሚያሳዩት ትርኢት አንዱና ዋነኛው ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አዳብና ላይ ወንዶች ተሳታፊዎች “አጋት”የሚባል ጨዋታ ይጫወታሉ። በመጀመሪ አንድ ተጫዋች ከፊት ለፊት ቀጥ ብሎ ይቆማል ።ሌላኛው ተጫዋቹ ደግሞ በግምት ከ20 ሜትር አካባቢ በመንደርደር የቆመውን ተጫዋች ከእጁ በስተቀር ትክሻውና ጭንቅላቱ ሳይነካ ዘሎ ያልፋል። ተጫዋቱ ጭንቅላቱን ሳይነካ ማለፍ ካቃተው ተረኛ ቋሚ ይሆናል።ማለፍ ከቻለ ግን ቆሞ የነበረው ተጫዋች ትክሻ ላይ ወጥቶ በመቀመጥ ሎሚ ወደ ላይ ይወረውራል።እሷን ሎሚ ተሻምቶ የያዘ ሰው የሚቀጥለው ዘላይ ተጫዋች ይሆናል።



ሌላው አዳብና ጨወታ ላይ ወንዶችና ልጃገረዶች ለትዳር አጋርነት የሚተጫጩበት ወቅትና ቦታ ነው ማለት ይቻላል። ወንዱ በጨዋታው መሃል ቀልቡ ያረፈባት ኮረዳ(ቀንዠ) ካየ ከኮረዳዋ በኋላ በኩል ሄዶ ቀሙሷን በያዘው አለንጋ መታ ያደርጋታል።በዚህ ጊዜ ኮረዳዋ ቀሚሷን በአንጋ የገረፋት ጎረምሳ እንደመረጣትና እንደወደዳት በመረዳት ትሽኮረመማለች ። አንዳንዴም ጭራሹኑ ልታለቅስ ትችላለች። ወንድዬውም በዚህ ብቻ አያበቃም የወደዳትን ልጃገረድ(ቀንዠ) ቀስ ብሎ በጓደኞቿ በኩል ሎሚ ወይም ማስቲካ ይልክላታል። ከተቀበለች እሷም ወደዋለች ተስማምታለች ማለት ነው። አልያም ፈሪና አይን አፋር ከህነ ደፋር ጓደኛ ከመሃል አይጠፋምና በጓደኛውም ሊያስጠይቃት ይችላል ከዚህ በኋላ ወንድዬው የትዳር አጋሩ እንድትሆን ከፈለገ ጎሳዋንና (በጉራጌ የጋብቻ ስርዓት ተመሳሳይ ጎሳ ስለማይጋባ) አካባቢዋ ካጣራ በኋላ እንድትለመንለት (እንድትታጭለት) ለቤተሰቦቹ ይናገራል። ቤተሰቦቹም ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ሽማግሌ ይልካሉ።የሽማግሌዎቹ ልመና ተቀባይነት ካገኘ በዛው አመት ጥሎሽ (ቸግ) ይጣላል። ቸግ(ጥሎሽ) ከጣለ በኋላ ነገርዬው ህጋዊ ሆነ ማለት ነው።ምን አልባት በሰርግ እስኪጋቡ ድረስ በእጮኝነት ከአንድ እስከ ሶስት ዓመት ሊቆዩ ይችላሉ ።እስከዛው አዳብና ላይ እየተገናኙ ይጫወታሉ፣ ስጦታ ይሰጣጣሉ። ከተጋቡ በኋላ ግን በዓመታቸው የመጨረሻው አዳብና አክብረው አዳብና መሄድ ያቆማሉ።



የአዳብና ክብረ በዓል ካለው ፋይዳዎች ጥቂቶቹ
- ለአቅመ ሂዋንና አቅመ አዳም የደረሱ ሴቶችና ወንዶች የሚተጫጩበትና ራሳቸውን ለጋብቻ የሚያዘጋጁበት፣ ለዚህም ሲሉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ባህላዊ አልባሳትን ከማዘጋጃጀት ጀምሮ ፀጉራቸው ሌሎችን ጌጣጌጦችን በማድረግ አዳብናን ለማድመቅ በጭፈራ ወደ ገበያ ያመራሉ
የተለያዩ የባህል እስፖርቶች በወጣቶች ዘንድ የሚካሄድበት( አጋት,የምድር ዝላለ ወይም እላፊ,ሰባ እና የመሳሰሉትን) እነዚህም የባህል አስፖርቶች በማህበረሰቡ ዘንድ አሮጌውን ዘመን አልፈው አዲሱን ዘመን መቀበላቸውን የሚያበስሩበት መሆኑን ያመላክታል።
ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ የቤተሰብ አባላትና ዘመዳሞች የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትና የሚረዳዱበት፣
የመስቀል በዓልን ምክንያት በማረግ የተጣሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና በጥል የተለያዩ ወጣቶች በአጠቃላይ በተለያየ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት እርቅ የሚወርድበትና ሰላም የሚሰፍንበት እንዲሁም በማህበረሰቡ አባላት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በዓሉ የጎላ ድርሻ የሚያበረክት መሆኑ፤
እንደቤተሰብና አካባቢ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚሰሩ ስራዎች ተለይተው እንዴት መሰራት እንዳለባቸው የሚመከርበትና የሚታቀድበት እንዲሁም በአንዳንድ ባህሉን የሚያጠናበት፣ የሚለዋወጥበት ወቅት መሆኑ፤
በአጠቃላይ የአዳብና ክብረ በዓል ከባህላዊ ትርጉምና ሥርዓቱ ባሻገር በሶዶ ክስታኔዎች ዘንድ ጥልቅ የሆነ የመተሳሰብ፣ የፍቅር፣ የወዳጅነት መንፈስ የሚጎለብትበት ወቅት ነው፡፡