አክራሚ (እንቁጣጣሽ)
አክራሚ (እንቁጣጣሽ) በክስታኔ ጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ እጅግ የተከበረ በዐል ነው።በክስታኔ አብዛኛው ህዝብ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን በዐሉ ኀይማኖታዊ ይዘቱን እና ባህላዊውን የበዓል አከባበር አጣምሮ የሚከበር በዐል ነው።በበዓሉ ዋዜማ ከሚከወኑ ነገሮች መካከል “ቄጤማ” ነው።ቄጤማ ታጭዶ የሚዘጋጀው በበዓሉ ዋዜማ ዕለት ነው።በበዓሉ እለት ለበዓሉ ማድመቂያ ይሆን ዘንድ ቤት ውስጥ መሬት ላይ የሚጎዘጎዝ ሲሆን “እንጊጫ” ተብሎ የሚጠራው ሳር መሰል ነገርም የሚታጨደው በዚሁ በበዐል ዋዜማ ነው።እንጊጫ የሚዘጋጀው በበዐሉ እለት ዘመን መለወጫን በማስመልከት ጭንቅላት ላይ የሚታሰር ነገር ነው።
ይኼ ሳር መሰል ነገር ቁመቱ ከአርባ እስከ ሃምሳ ሳንቲም የሚረዝም ሲሆን በበዐሉ እለት ቤተክርስቲያን ወስደው በቄሳውስት አስባርከው ወደ ቤት አምጥተው ጭንቅላታቸው ላይ ያስሩታል።ማህበረሰቡ ከ90% በላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይም ስለሆነ የአክራሚ (እንቁጣጣሽ) እለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን በየአመቱ በአዲስ አመት ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ አመቱን ሙሉ ዘመነ (ማቴዎስ፣ማርቆስ፣ሉቃስና ዮሐንስ) እየተባለ ስለሚጠራ በአክራሚ እለት የሶዶ ክስታኔ ጉራጌ ህዝብ ሁሉም በሚባል ደረጃ በቅርብ ወደሚገኝ ወንዝ ሄዶ ከታጠበ በኋላ ቀጥሎም ፀበል ተጠምቆ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ሄዶ ተረኛውን ወንጌላዊ አንግሶ ወደ ቤቱ ሲመለስም በተለመደው በክስታኔ ጉራጌ ባህል መሠረት የተዘጋጀ ቅንጬ በቅቤ ተበልቶ ሀ ብሎ የአክራሚ የበዐል ቀን ውሎ ይጀምራል።

በመቀጠልም ዕለቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይታሰባል ለአብነትም በምሳ ሰዐት (እቆት በአልቤቤጫት) በቦሌ የተቀቀለ ጎመን በአይብና በቆጮ ጎረቤቶች ተጠራርተው ይበላሉ በዛውም ሁሉም እንደየ አቅሙ የሚታረድ ነገር አዘጋጅቶ ተመርቆ ቅቤ ተቀብቶ ይታረዳል ይበላል ይጠጣል ቀኑ የተለየ ደስታ የሚታይበት እጅግ አስደናቂ ቀን ነው።
አክራሚ ንዎደድትን አመትባለ
እንኳን አሰላንህም
እንኳን አደረሳችሁ

