ባለ ዋሻው የሰረገላ_ገዳም ምድረ ከብድ!

በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ወደ ቡታጅራ በሚወስደው ዋና መንገድ ከቡኢ ከተማ በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከፅኑ የፆምና ፀሎት ተጋድሎ በኋላ ያረፉበት፤ የአፅማቸው መገኛ ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በሰረገላ ተጭነው ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲመጡ መጀመሪያ ያረፉት በምድረ ከብድ ነበር። አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ 562 ዓመት የኖሩ ሲሆን በምድረ ከብድ ብዙ ፈተናዎች ተጋፍጠው የድል አክሊል ተቀዳጅተዋል። ምድረከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም በአመት ሁለት ጊዜ ይከበራል። ጥቅምት አምስት እና መጋቢት አምስት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች እና ሌሎች ጎብኚዎች ይታደማሉ ። በገዳሙ እምነት፣ እውቀት እና ትጋት ተዳምረው ያስገኙት ወጤት መመልከት በጎብኚዎች ዘንድ አንዳች የደስታ ስሜት ያጭራል። በገዳሙ ለጥናትና ምርምር የሚያግዙ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች እና የተለያዩ የልማት ስራዎች በስፋት ይታያሉ ።

ስያሜው ምድረ ከብድ ነው፡፡ የገዳሙ አባቶች የስሙን ትርጉም ጽኑ ቦታ፣ ከባድ ስፍራ፣ ከፍ ያለ በረከት የሚገኝበት፣ ሆደ ሰፊና ቻይ በሚሉ ትርጓሜዎች ያብራሩታል፡፡ ሁሉንም ላሉበት የራሳቸውን ተከታይ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ስብር ያሉና ትሁት ኢትዮጵያውያን አባቶችን እየተመለከትኩ ነው፡፡ ሊያውም ነገ አቡዬን ሊያነግሱ ውጥረት ላይ ሆነው እንጂ በአዘቦትም ከእንግዳ እግር ስር መች ተነስተው፤ ስፍራውን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንደመሰረቱት ታሪኩ ይናገራል፡፡የምድረ ከብድ አቦ ገዳም በአብነት (መንፈሳዊ) ትምህርት ስርጭቱ ይታወቃል፡፡ ከሚሰጡትም መንፈሳዊ ትምህርቶች የንባብ ቤቶች፣ የዜማቤት፣ የቅኔ ቤት ወዘተ መጠቃቀስ ይቻላል፡፡

 የክቧ ቤተ ክርስቲያን ደጀንም ዛፎቿ ናቸው፡፡ በሸዋ ከሚገኙ የአብነት ትምህርት ማዕከላት አንዱ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኗ ኋላ ከተዳፋታማው ስር የሚገኝ ዋሻ አለ፡፡ ምድረ ከብዶች ይህ ዋሻ ዝቋላ እንደሚያደርስ ያምናሉ፡፡ ምድረ ከብድ በርካታ ጥንታዊ የብራና ቅዱሳት መጻህፍት የሚገኝበት ጥንታዊ ስፍራ ነው፡፡ ጥቅምት አምስት ቀን የመጣ ደግሞ ተአምር ይመለከታል፡፡ ይህው ዋዜማውን የጉራጌ መንደሮች ሽርጉድ እያሉ ነው፡፡